The Noble Qur'an Encyclopedia
Towards providing reliable exegeses and translations of the meanings of the Noble Qur'an in the world languagesSaba [Saba] - Amharic translation - Africa Academy
Surah Saba [Saba] Ayah 54 Location Maccah Number 34
1. ምስጋና ሁሉ ለዚያ በሰማያትም ያለው በምድርም ያለው ሁሉ የእርሱ ለሆነው ለአላህ ብቻ ይገባው:: በመጨረሻይቱም ዓለም ምስጋና ሁሉ ለእርሱ ብቻ ነው:: እርሱም ጥበበኛና ውስጠ አዋቂው ነው::
2. አላህ በምድር ውስጥ የሚገባውን ሁሉ ከእርሷ የሚወጣውንም ከሰማይም የሚወርደውን በእርሷ ውስጥ የሚያርገውንም ሁሉ ያውቃል:: እርሱም አዛኝና መሃሪ ነው::
3. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያ በአላህ የካዱትም ሰዎች «ሰዓቲቱ አትመጣብንም» አሉ፡ «ጉዳዩ እንዳሰባችሁት አይደለም። ሩቁን ሁሉ አዋቂ በሆነው ጌታዬ እምላለሁ:: በእርግጥ ትመጣባችኋለች:: የብናኝ ክብደት ያክል እንኳ በሰማያትና በምድር ውስጥ ከእሱ አይሰወርም አይርቅም:: ከዚህ ያነሰም ሆነ የበለጠ የለም በግልጹ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ ቢሆን እንጂ::» በላቸው
4. እነዚያን ያመኑትንና መልካም የሰሩትን ሊመነዳ ሰዓቲቱ ትመጣባችኋለች:: እነዚያ ለእነርሱ ምህረትና የከበረ ሲሳይ አለላቸው::
5. እነዚያም የሚያመልጡ መስሏቸው አናቅጻችንን ለማፍረስ የጣሩ እነዚያ ለእነርሱ ከመጥፎ ቅጣት የሆነ አሳማሚ ስቃይ አለባቸው::
6. እነዚያም እውቀትን የተሰጡት ያንን ከጌታህ ወደ አንተ የተወረደውን እውነትና አሸናፊ ምስጉን ወደ ሆነው የአላህ መንገድ የሚመራ መሆኑን ያውቃሉ::
7. እነዚያም በአላህ የካዱት አሉ: «(ሙታችሁ) ሙሉ መበጣጠስን በተበጣጠሳችሁ ጊዜ በአዲስ መፈጠር ውስጥ ትሆናላችሁ ብሎ የሚነግራችሁን ሰው እናሳያችሁን?
8. «በአላህ ላይ ውሸትን ቀጠፈን? ወይስ በእርሱ እብደት አለበት?» አሉ:: እንዳሉት አይደለም። እነዚያ በመጨረሻይቱ ዓለም የማያምኑት በእርሷ በቅጣት ውስጥ የሚሆኑና አሁንም በራቀ ስህተት ውስጥ ናቸው::
9. ከሰማይና ከምድር በፊታቸውና በኋላቸው ወደ አለው ሁሉ አይመለከቱምን? ብንሻ እኮ በእነርሱ ምድርን እንደረምስባቸዋለን :: ወይም በእነርሱ ላይ ከሰማይ ቁራጭን እንጥልባቸዋለን:: በዚህ ውስጥ ወደ ጌታው ተመላሽ ለሆነ ባሪያ ሁሉ ታላቅ ምልክት አለበት፡
10. ለዳውድም ከእኛ የሆነን ችሮታ በእርግጥ ሰጠነው:: (አልንም) ተራራዎች ሆይ! ከእሱ ጋር ውዳሴን መላልሱ:: በራሪዎችንም (ገራንለት)። ብረትንም ለእሱ አለዘብንለት::
11. ሰፋፊዎችን ጥሩሮዎች ስራ:: በአሰራርዋም መጥን:: መልካምንም ስራ ስሩ:: እኔ የምትሰሩትን ነገር ሁሉ ተመልካች ነኝና (አልነው)::
12. ለሱለይማንም ንፋስን የቀትር በፊት ጉዞዋ የወር መንገድ፤ የቀትር በኋላ ጉዞዋም የወር መንገድ ሲሆን ገራንለት:: የነሀስንም ምንጭ ለእርሱ አፈሰስንለት:: ከአጋንንቶችም በጌታው ፈቃድ በፊቱ የሚሰሩትን (አደረግንለት):: ከእነርሱም ውስጥ ከትእዛዛችን ዝንፍ የሚል ከነዳጅ እሳት ቅጣት እናቀምሰዋለን::
13. ከምኩራቦች፤ ከምስሎችም እንደ ገንዳ ከሆነ ገበታዎችም፤ ከተደላደለ ታላላቅ ድስቶችም የሚሻውን ሁሉ ይሰሩለታል፣ (አልናቸዉም:) «የዳውድ ቤተሰቦች ሆይ! በጣም አመስጋኞች ሆናችሁ ለጌታችሁ ስሩ::» ከባሮቼ ውስጥ አመስጋኞቹ ጥቂቶች ናቸው::
14. በእርሱም ላይ ሞትን በፈጸምንበት ጊዜ መሞቱን ብትሩን የምትበላ ተንቀሳቃሽ ምስጥ እንጂ ሌላ አላመለከታቸዉም:: በወደቀ ጊዜም አጋንንቶች ሩቅን ሚስጥር የሚያውቁ በሆነ ኖሮ በአዋራጅ ስቃይ ውስጥ የማይቆዩ እንደነበሩ ተረዱ::
15. ለሰበእ ነገዶች በመኖሪያቸው በእውነት አስደናቂ ምልክት ነበራቸው:: ከግራና ከቀኝ ሁለት አትክልቶች ነበሯቸው:: «ከጌታችሁ ሲሳይ ብሉ ለእሱም አመስግኑ:: አገራችሁ ውብ አገር ናት:: ጌታችሁም መሃሪ ጌታ ነው» ተባሉ::
16. አላህን ከማመስገን ዞሩም:: በእነርሱም ላይ የግድቡን ጎርፍ ለቀቅንባቸው:: በሁለቱ አትክልቶቻቸዉም ሌሎች ሁለትን አትክልቶች ባለ መርጋጋ ፍሬዎችን ባለ ጠደቻና ከቁርቁራም ባለ ጥቂት ዛፎችን ለወጥናቸው::
17. በመካዳቸው ምክንያት ይህንን መነዳናቸው:: (እንደዚህ ያለውን ቅጣት) በጣም ከሓዲ ለሆነ ሰው ብቻ እንጂ ለሌላው እንሰጣለን?
18. በእነርሱና በዚያች በውስጧ በረከትን ባደረግንባት አገር (በሻም) መካከልም ተከታታይ መንደሮችን (ቅጥልጥል ከተሞች) አደረግን:: በእርሷም ጉዞን ወሰንን። «በሌሊቶችም ሆነ በቀኖች ዉስጥ ጸጥተኞች ሆናችሁ ተጓዙ» (አልን)::
19. «ጌታችን ሆይ! በጉዞዎቻችን መካከል አራርቅልን» አሉም:: ነፍሶቻቸውንም በደሉ:: መገረሚያ ወሬዎችም አደረግናቸው:: መበታተንንም ሁሉ በታተንናቸው:: በዚህ ውስጥ በጣም ታጋሽና አመስጋኝ ለሆነ ሁሉ ብዙ መገለጫዎች አሉበት::
20. ዲያብሎስም በእነርሱ ላይ ምኞቱን በእርግጥ ፈጸመ:: እናም ከአመኑት የሆኑት ቡድኖች በስተቀር ተከተሉት::
21. በመጨረሻይቱም ዓለም የሚያምነውን ከዚያ እርሱ ከእርሷ በመጠራጠር ውስጥ ከሆነው ሰው ለይተን እንድናውቅ እንጂ በእነርሱ ላይ ለእርሱ ምንም ስልጣን አልነበረዉም:: ጌታህም በነገሩ ሁሉ ላይ ተጠባባቂ ነው::
22. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እነዚያን ከአላህ ሌላ አማልክት ብላችሁ የምታስቧቸውን ጥሩ:: በሰማያትም ሆነ በምድር ውስጥ የብናኝ ክብደት ያህል እንኳ ምንም አይችሉም:: ለእነርሱም በሁለቱም ውስጥ ምንም ሽርክና የላቸዉም:: ከእነርሱም ለእርሱ ምንም አጋዥ የለዉም።» በላቸው::
23. ምልጃም እርሱ ለፈቀደለት ሰው ብቻ ቢሆን እንጂ እሱ ዘንድ ምንም አትጠቅምም:: ከልቦቻቸው ላይ ድንጋጤው በተገለጠ ጊዜ ተማላጆቹ «ጌታችሁ ምን አለ?» ይላሉ:: አማላጆቹም: «እውነትን አለ። እርሱም ከፍተኛውና ታላቁ ጌታ ነው።» ይላሉ::
24. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ)፤ «ከሰማያትና ከምድር ሲሳይን የሚሰጣችሁ ማነው?» በላቸው። «አላህ ነው እኛ ወይም እናንተ በትክክለኛው መንገድ ላይ ወይም በግልጽ መሳሳት ውስጥ ነን።» በላቸው።
25. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ !)«ካጠፋነው ጥፋት አትጠየቁም:: ከምትሰሩትም ስራ አንጠየቅም።» በላቸው::
26.(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ጌታችን በመካከላችን ይሰበስባል። ከዚያም በመካከላችን በእውነት ይፈርዳል:: እርሱም በትክክል ፈራጁና አዋቂው ነው።» በላቸው።
27.(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እነዚያን ተጋሪዎች አድርጋችሁ በእሱ ያስጠጋችኋቸውን ጣዖታት እስቲ አሳዩኝ:: ተው አታጋሩ:: በእውነት እርሱ አሸናፊዉና ጥበበኛው አላህ ነው።» በላቸው::
28. አንተንም ለሰዎች ሁሉ በመላ አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን ቢሆን እንጂ አልላክንህም:: ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም::
29. «እውነተኞችም እንደ ሆናችሁ ይህ ቀጠሮ መቼ ነው?» ይላሉ::
30. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ለእናንተ ከእርሱ አንዳችንም ሰዓት የማትዘገዩበት የማትቀድሙበትም የቀጠሮ ቀን አላችሁ።» በላቸው::
31. እነዚያም የካዱት «በዚህ ቁርኣንና በዚያ ከበፊቱ ባለዉም መጽሐፍ በጭራሽ አናምንም።» አሉ:: በዳዮችም ከፊላቸው ወደ ከፊሉ ንግግርን የሚመላላሱ ሆነው በጌታቸው ዘንድ በሚቆሙ ጊዜ ብታይ ኖሮ አስደናቂን ነገር ታይ ነበር:: እነዚያ የተዋረዱት ለእነዚያ ለኮሩት «እናንተ ባልነበራችሁ ኖሮ ትክክለኛ አማኞች በሆንን ነበር።» ይላሉ::
32. እነዚያ የኮሩት ለእነዚያ ለተዋረዱት «ትክክለኛው እምነት ከመጣላችሁ በኋላ እኛ ከለከልናችሁን? አይደለም:: እናንተው ከሓዲያን ነበራችሁ።» ይሏቸዋል።
33. እነዚያም የተዋረዱት ለእነዚያ ለኮሩት «አይደለም። በአላህ እንድንክድና ለእርሱ ባላንጣዎችን እንድናደርግ ስታዙን (የከለከለን) የሌሊትና የቀን ዱለታችሁ ነው።» ይላሉ:: ቅጣትንም ባዩ ጊዜ ጸጸትን ይደብቃሉ:: በእነዚያም በካዱት አንገቶች ላይ እንዛዝሎችን እናደርጋለን:: ይሰሩት የነበሩትን እንጂ ሌላን ይመነዳሉን?
34. በየትኛዋም ከተማ አስፈራሪን አላክንም ነዋሪዎችዋ «እኛ በተላካችሁት ከሓዲያን ነን።» ያሉ ቢሆኑ እንጂ::
35. «እኛም በገንዘቦችና በልጆች ይበልጥ የበዛን ነን:: እኛም የምንቀጣ አይደለንም» አሉ::
36. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ጌታዬ ሲሳይን ለሚሻው ሰው ሁሉ ያሰፋል:: ለሚሻው ሰዉም ሁሉ ያጠባል:: ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች ይህን አያውቁም።» በላቸው።
37. ገንዘቦቻችሁና ልጆቻችሁም ያች እኛ ዘንድ መቅረብን የምታቀርባችሁ አይደለችም:: ያ በትክክል ያመነና መልካምን የሰራ ብቻ ሲቀር:: እነዚያ ለእነርሱ በሰሩት መልካም ስራ እጥፍ ምንዳ አለላቸው:: እነርሱም በገነት ሰገነቶች ውስጥ ጸጥተኞች ናቸው።
38. እነዚያም የሚያቅቱ መስሏቸው አናቅጻችንን ለማበላሸት የሚጥሩ ሁሉ እነዚያ በቅጣት ውስጥ የሚጣዱ ናቸው::
39. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ጌታዬ ሲሳይን ከባሮቹ ለሚሻው ሰው ያሰፋል:: ለእርሱም ያጠባል:: ከማንኛዉም ነገር የምትለግሱትን እርሱ ይተካዋል:: እርሱም ከሲሳይ ሰጪዎች ሁሉ በላጭ ነው።» በላቸው።
40. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ሁሉንም በሚሰበስባቸውና ከዚያም ለመላእክቶቹ «እነዚህ እናንተን ይገዙ ነበሩን?» በሚላቸው ቀን የሚሆነውን አስታውስ::
41. መላእክቶቹም «ጥራት ይገባህ ረዳታችን ከእነርሱ ሌላ የሆንከው አንተው ብቻ ነህ:: እንደሚሉት አይደለም:: ይልቁንም አጋንንትን ይገዙ ነበሩ:: አብዛኞቻቸው በእነርሱ አማኞች ናቸው።» ይላሉ።
42. ዛሬም ከፊላችሁ ለከፊሉ መጥቀምንም ሆነ መጉዳትን አይችሉም:: ለእነዚያም ለበደሉት ሰዎች «ያችን በእርሷ ታስተባብሉባት የነበራችሁትን የእሳት ቅጣት ቅመሱ» እንላቸዋለን::
43. በእነርሱም ላይ አናቅጻችን ግልጽ ሆነው በተነበቡላቸው ጊዜ «ይህ አባቶቻችሁ ይገዙት ከነበሩት ነገር ሊከለክላችሁ የሚፈልግ ሰው እንጂ ሌላ አይደለም።» አሉ:: «ይህም ቁርዓን የተቀጣጠፈ ውሸት ነው እንጂ ሌላ አይደለም።» አሉም። እነዚያም በአላህ የካዱት እውነትን በመጣላቸው ጊዜ «ግልጥ ድግምት ነው እንጂ ሌላ አይደለም።» አሉ።
44. የሚያጠኗቸው የሆኑ መጽሐፎችንም ምንም አልሰጠናቸዉም:: ካንተ በፊትም አስፈራሪ ነብይን ወደ እነርሱ አልላክንም::
45. እነዚያም ከእነርሱ በፊት የነበሩት አስተባብለዋል:: የሰጠናቸውንም ከአስር አንዱን እንኳን እነዚህ አልደረሱም:: እናም መልዕክተኞቼን አስተባበሉ:: ነቀፍኳቸዉም:: መንቀፌም እንዴት ነበር::
46. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «የምገስጻችሁ በአንዲት ነገር ብቻ ነው:: እርሷም ሁለት ሁለት፤ አንድ አንድም ሆናችሁ ለአላህ እንድትነሱና ከዚያም በጓደኛችሁ (በሙሐመድ) ምንም እብደት የሌለበት መሆኑን መርምራችሁ እንድትረዱ ነው:: እርሱ ለእናንተ ከብርቱ ቅጣት በስተፊት አስጠንቃቂ ነው እንጂ ሌላ አይደለም።» በላቸው።
47. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ከዋጋ ማንኛውንም የጠየቅኋችሁ ቢኖር እርሱ ለእናንተው ነው:: ዋጋዬ በአላህ ላይ እንጂ በሌላ ላይ አይደለም:: እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ አዋቂ ነው።» በላቸው።
48. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ጌታዬ እውነትን ብቻ ያወርዳል:: ሩቅ የሆኑትን ምስጢሮች ሁሉ አዋቂ ነው።» በላቸው።
49. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እውነቱ መጣ ውሸት መነሻም መድረሻም የለዉምና ተወገደ።» በላቸው።
50. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ብሳሳትም የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው:: ብመራም ጌታዬ ወደ እኔ በሚያወርደው መመሪያ መሰረት ነው:: እርሱ ሁሉ ሰሚና ለሁሉም ቅርብ ነውና።» በላቸው::
51. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) በደነገጡና ማምለጫ በሌላቸው ጊዜ ከቅርብ ስፍራም በተያዙ ጊዜ ሁኔታቸውን ብታይ ኖሮ (አስደናቂን ነገር ባየህ ነበር)::
52. «በእርሱም አሁን አመንን።» ይላሉ:: ለእነርሱም ከሩቅ ስፍራ እምነትን በቀላሉ ማግኘት ከየታቸው ይታደሉና?
53. በፊትም በእርሱ በእርግጥ ክደዋል:: ከሩቅ ስፍራም በግምት ንግግርን ይጥላሉ::
54. ከዚህ ቀደም በመሰሎቻቸው እንደተሰራዉም ብጤ በእነርሱና በሚፈልጉት መካከል ተጋረደ:: እነርሱ በእርግጥ በአወላዋይ ጥርጣሬ ውስጥ ነበሩና::